ቡና ለመጠጣት መንገድ ሲያቋርጥ ባጋጠመው አደጋ ህይወቱ የተመሳቀለው ወጣት - bbc news አማርኛ

feature-image

Play all audios:

Loading...

ቡና ለመጠጣት መንገድ ሲያቋርጥ ባጋጠመው አደጋ ህይወቱ የተመሳቀለው ወጣት 19 ሚያዚያ 2021 የከባድ መኪና አሽከርካሪው አዲስ ዘመን እግረኛ ሆኖ መንገድ ሲያቋርጥ የገጠመው የትራፊክ አደጋ አምስት ዓመታት በሆሰፒታል አልጋ የስቃይ ጊዜያትን እንዲያሳልፍ አስገድዶታል። የደረሰበትን ጉዳት አስራ አራት


ጊዜ ከባድ ቀዶ ህክምና እንዲያደርግና ለህክምና ገንዘብ ተቸግሮ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ለልመና እንዲቀመጥም ምክንያት ሆኗል። የመከላከያ ሠራዊት አባል የነበረው አዲስ ከባድ መኪና እያሽከረከረ በሚያገኘው ገቢ 15 ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ህይወቱን መርቷል። ከስድስት ዓመታት በፊት ያጋጠመው ክስተት ግን


የህይወቱን መሰመር እስከ ወዲኛው የቀየረ ነበር። ኅዳር 15/1999 ዓ.ም በመቶች የሚቆጠር ኪሎ ሜትሮችን ተጉዞ ከደሴ በቅርብ ርቀት ወደምትገኘው ኩታበር ከተማ ሲደርስ ለእርፍት አቆመ። እንደእሱ የከባድ መኪና አሽከርካሪ ከሆነው ጓደኛው ጋር ሲጫወቱ ቆይተው ቡና ለመጠጣት በእግራቸው መንገድ ማቋረጥ


ጀመሩ። እናም በመንገዳቸው መካከል ያልታሰበው ሆነ። Skip ብዙ የተነበቡ and continue reading ብዙ የተነበቡ * በሶማሌ ክልል "የመገንጠል ስሜት ቀርቷል ማለት ይቻላል" - ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ መሐመድ * አፍሪካውያን ስለ ትራምፕ አዲሱ የጉዞ ዕገዳ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች *


ተቃዋሚዎች ትራምፕ ካሰማሯቸው ወታደሮች ጋር የተፋጠጡባት ሎስ አንጀለስ * በዓለም ዙሪያ የሚሊዮኖችን ቀልብ ሰቅዘው የያዙት የአንድ ደቂቃ የቻይና ድራማዎች End of ብዙ የተነበቡ "በአጋጣሚ ዞር ስል አንድ ፒክ አፕ መኪና መሪው ግራና ቀኝ እየዋለለ በቅጽበት ሲመጣ አየሁ። ከእኔ ጋር


የነበረውን ሹፌር ጓደኛዬን ገፈተርኩትና እኔም በተቃራኒ አቅጣጫ ሸሸሁ። ከአስፓልቱ ከአስር ሜትር በላይ ሩጫያለሁ። ግን አላመለጥኩም መኪናው ሦስት ቦታ ላይ መታኝ" ሲል የነበረውን አሰቃቂ ክስተት አዲስ ያሰታውሳል። በአደጋውም መጀመሪያ እግሩን የመኪናው የፊተኛ ክፍል ሲመታው ወደቀ ከዚያም


የእጎተተ ሲወስደው ደርቱና አንገቱ ላይ ከባድ ጉዳት አደረሰበት። "ከዚያ በኋላ የሆነውን አላውቅም" ይላል። "እሰኪ አስነዳኝ!" ያስከተለው መዘዝ አዲስ ላይ ይህንን አደጋ ያደረሰው አሽከርካሪ በቂ ልምድ ያልነበረው ሲሆን "እስኪ አስነዳኝ!" በሎ ከሾፌሩ


ተቀብሎ መሪ የጨበጠ የመኪና ባለቤት ነው። ልምድ ያለው አሽከርካሪ ቢሆን ኖሮ "ብዙም ጉዳት አይደርስብኝም ነበረ" ሲል የሚናገረው አዲስ፤ ለአደጋው መባባስ የአሽከርካሪውን ልምድ ማነስ ዋናኛ ምክንያት ነው ይላል። "መለማመድ ካለበት እኮ ትምህርት ቤቶች አሉ። አደጋ ማይበዛበት


ቦታ ላይ ከፍሎ መንዳት ይችል ነበር። የእኔን ህይወት ያየ ድጋሚ ልምድ ለሌለው ሰው መኪና ይሰጣል ብዬ አላምንም" ሲል ተናግሯል። * በኢትዮጵያ በስድስት ወራት ከሃያ ሺህ በላይ የትራፊክ አደጋ ማጋጠሙ ተገለፀ * በምሥራቅ ጎጃም በደረሰ የትራፊክ አደጋ የ30 ሰዎች ህይወት አለፈ ለአምስት


ዓመታት በሦስት ሆስፒታሎች ህክምናውን ሲከታተል የቆየው አዲስ 14 ጊዜ ቀዶ ህክምና ተደርጎለታል። በአደጋው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው የሰውነቱ ክፍሎች ውስጥ 'ብረት' ወይም Plate ተደርጓል። ጉልበቱ አይታጠፍለትም፣ ረጅም መንገድ መጓዝ አይችልም፣ ሲራመድም ያነክሳል። ከአደጋው ጋር


በርካታ ነገሮቹ ተመሰቃቅለዋል "እግሬ ኢንፌክሽን ፈጥሮ መንገድ ዳር ቁጭ ብዬ የአዲስ አበባን ሕዝብ አንድ ብርና ሃምሳ ሳንቲም ለምኜ ታክሜያለሁ" የሚለው አዲስ፤ ጉዳቱን ያደረሰበት ግለሰብ በሌላ ሰው አማካይነት ሁለት ጊዜ የህክምና ወጪውን ቢሸፍንለትም ከዚያ በኋላ ተሰውሮበታል።


ከአደጋው ጋር በተያያዘ የመንገድ ፈንድ ጽህፈት ቤት 40 ሺህ ብር ቢከፍለውም የህክምና ወጪውን ከዚህም በላይ ሆኖ አቅሙን ፈትኖታል። 17 አዳሪ ት/ቤቶችን ሊገነባ የሚችል ንብረት ወድሟል በኢትዮጵያ በትራፊክ አደጋዎች ሳቢያ የተፈጠሩ ከአዲስ ዘመን ጋር የሚመሳሰሉ ታሪኮች በርካታ ናቸው። ቁጥራቸውም


ከዕለት እለት እየጨመረ የሚሄድ ነው። በመገናኛ ብዙሃን በየቀኑ ከሚደመጡ የትራፊክ አደጋ ዘገባዎች ጀርባ የተናጉ ቤቶች፣ የተመሰቃቀሉ ህይወቶችና ከህመም ስቃይ ጋር እያንዳንዱን ቀን የሚያሳልፉ ዜጎች በርካቶች ናቸው። ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የተገኘ መረጃ እንደሚጠቁመው በተያዘው ዓመት የመጀመሪያ ስድስት


ወራት ውስጥ ብቻ የትግራይና የሲዳማ ክልልን ሳይጨምር በመላው አገሪቱ 1 ሺህ 849 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸው አልፏል። ይህ ቁጥር ከቫቲካን ከተማ ጠቅላላ ሕዝብ በእጥፍ የሚልቅ ነው። ከ 2 ሺህ 600 በላይ ሰዎች ከባድ ከ2 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።


የወደመው ንብረት ግምት ደግሞ ከ495 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ነው። ይህ ገንዘብ በቅርቡ ከ29 ሚሊዮን ብር በላይ በደሴ ከተማ የተገነባውን አይነት 17 ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን መገንባት የሚስችል ነው። በትራንስፖርት ሚኒስቴር የመንገድ ደኅንነት ምክር ቤት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮናስ በለጠ


የትራፊክ አደጋ 'አምራችና የተማረ' የሚባለውን የኅብረተሰብ ክፍል በብዛት እየቀጠፍ እንደሚገኝ ይናገራሉ። በሌላ በኩል በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የአጥንት ህክምና ክፍል ኃላፊውና የአጥንትና አደጋዎች ህክምና ስፔሻሊስቱ ዶ/ር ብሩክ ላምቢሶ የትራፊክ አደጋ በጤና ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ ጫና


እያሳደረ እንደሚገኝ ያስረዳሉ። "72 በመቶው በትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች የተያዘ ነው" ዶ/ር ብሩክ የትራፊክ አደጋ በህክምናው ላይ ያለውን ተጽእኖ ሲያስረዱ ከለጋሾች የሚሰበሰበውን ደም በመጠቀስ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ውስጥ ያለውን ስርጭት ለአብነት ያነሳሉ። በወሊድ ወቅት የሚያጋጥም


እጥረትን ለማቃለል የሚቀርበው ደም "በአባዛኛው የመኪና አደጋ ተጠቂዎችን ህይወት ለማትረፍ ነው የምንጠቀመው" ይላሉ። በቁጥር በበረከቱ አደጋዎች ምክንያት የሚደርሰው ጫና አምቡላንስ ከመሻማት ጀምሮ በህክምና ክፍሉ ቀድመው የተያዙ የቀዶ ህክምና ቀጠሮዎችን እስከ ማሰረዝ ደርሰዋል።


"እኛ ባለን አሃዝ መሠረት በዓመት ውስጥ ከምንሰጠው የህክምና አገልግሎት ውስጥ 72 በመቶው የመኪና አደጋ ተጎጂዎች ናቸው። ስለዚህም ካለን ሃብት፣ ሙያ እና ጊዜ ውስጥ ሦስት አራተኛ የሚሆነው በመኪና አደጋ ተጎጂዎች ላይ የሚውል ነው።" ይህ አሃዝ ደግሞ የአንድና የሁለት ወይም የጥቂት


ዓመታት መረጃን መሠረት ያደረገ ሳይሆን በ30 ዓመታት የህክምና ሥራን የተከናወኑ አገልግሎቶችን በማስላት የተገኘ እንደሆነ ዶ/ር ብሩክ ገልጸዋል። የቀረውን ድርሻ ደግሞ የዲስክ ህመም ላለባቸው፣ በካንሰር ምክነያት ለአጥንት ችግር ለተጋለጡ፣ በስፖርትና በመውደቅ አደጋ ለተጎዱና መሰል ችግሮች የተተወ


ነው። "የመኪና አደጋው ሃብት ሰለሚሻማ ሌሎቹ [ከትራፊክ አደጋ ወጪ ያሉ የህክምና ክፍሉ ታካሚዎች] አልጋ የለም፣ ድንገተኛ ሞልቶበታል ይባላሉ - ይንከራተታሉ" ሲሉ አደጋው የፈጠረውን የዕለት ከእለት ጫናን ይገልጻሉ። "የሞቱት ይሻላሉ እስኪባል ድርስ በስቃይ የሚያልፉ ተጎጂዎች


አሉ።" "በእውነቱ ተርፏል ወይ የሚያሰኙ አደጋዎች ይገጥሙናል" ሲሉ የአንዳንዶቹን ጉዳት የሚያስረዱት ዶ/ር ብሩክ "ወጣት ዕድሜ ላይ ያሉ፣ የት ይደርሳሉ የተባሉ ልጆች እጃቸው ወይም እግራቸው ተቆርጦ፣ ጭንቅላታቸው ተመቶ አዕምሯቸው መስራት ሲያቆም ገጥሞናል።


"በትራፊክ አደጋ ምክንያት በሚደርስ ጉዳት መናገር ያቃታቸው፣ መራመድ የተሳናቸውና ፓራላይዝድ የሆኑ [ሰውነታቸው አልታዘ ሲላቸው]፤ ልጆች አባታቸው ጠዋት በሰላም ወጥቶ ዊልቼር ላይ ሆኖ ሲያዩት ሥነ ልቦናቸው እንዴት እንደሚጎዳ እናያለን። አንዳንዴ እንዲያውም የሞቱት ይሻላሉ እስኪባል ድርስ


በስቃይ የሚያልፉ ተጎጂዎች አሉ" ይላሉ። በትራፊክ አደጋ የሚደርሱ የእለት ከዕለት ሰቆቃዎችን የሚመለከቱት እንደ ዶክተር ብሩክ ያሉ ባለሙያዎችም የችግሩን ገፈት ይቀምሳል። የአደጋዎቹ ምክንያት ምንድን ናቸው? አቶ ዮናስ እንደሚሉት ከ40 በመቶ በላይ የትራፊክ አደጋዎች ምክንያት በፍጥነት


ማሽከርከር ነው። የሌሊት ጉዞ እንዲሁም ጠጥቶና አደንዛዥ ዕጽ ተጠቅሞ ማሽከርከር ሁለተኛው ምክንያት ሆኖ ተቀምጧል። እነዚህ ዋነኛ የአደጋ መንሰሄዎች ደግሞ ከሽከርካሪው ጋር በቀጥታ የሚያያዙ ናቸው ብለዋል። ሌላኛው ደግሞ የመንገዶች ምቹ አለመሆንን ይጠቅሳሉ። እናም 10 አደጋ ይበዛባቸዋል የተባሉና


2000 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ መንገዶችን 'የምህንድስና መፍትሄ' እንዲያገኙ "ጥናት አድርገን ለኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አስተላፈናል" የሚሉት ሃላፊው "ዋናው ጉዳይ ግን አሽከርካሪው ላይ ትልቅ ስራ መስራት እንደሚያስፈልገን ተረድተን ተከታታይ የሆነ የግንዛቤ


ማስጨበጫ እየሰራን ነው" ሲሉ ተናግረዋል። በለማጅ አሽከርካሪ ተገጭቶ ለዓመታት በስቃይ ውስጥ ያለፈው የቀድሞው ሾፌር አዲስ ዘመን አሁን በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ሥራ ጀምሯል። ሆኖም በእያንዳንዱ ቀን የሚሰማው ህመም ያለፉትን ጊዜያት ያስታውሰዋል። "አንድ ሰው ላይ የትራፊክ


አደጋ ስታደርስ ለአካል ጉዳት፣ ለስቃይ ወይም ለሞት የምታበቃው አንድን ሰው ብቻ አይደለም።ከእርሱ ባሻገር የሚረዳቸውን እናቱን ወይም አባቱን፤ የሚሳሳላቸውንና የሚለፋላቸውን ልጆቹን፣ እህት ወንድሞቹን ነው" ይላል። በጥንቃቄ ጉድለት ምክንያት በአንድ ሰው ላይ የሚደርሰው የትራፊክ አደጋ


ከጀርባው የበርካቶችን ተስፋ ያጨልማል፣ የሞቀ ቤትን ያቀዘቅዛል እንዲሁም ፈርጀ ብዙ ጉዳትን ያስከትላል። "ለእራሳችንም ለሌሎችም ደኅንነት ስንል በኃላፊነት እናሽከርክር" ይላል የትራፊክ አደጋ ህይወቱን ያመሳቀለበት አዲስ።